የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ዕድሜያቸው እስከ ሦስት ዓመት የሆኑ የሠራተኞቻቸውን ልጆች ማቆያ ማዕከላት እንዲያዘጋጁ የሚያስገድድ ረቂቅ አዋጅ መዘጋጀቱን ሰማን፡፡
የፐብሊክ ስርቪስና የሰው ኃብት ልማት ሚኒስቴር የመንግሥት ሠራተኞች ዕድሜያቸው እስከ ሦሰት ዓመት ያሉ ህፃናት የሚቆዩበት ማዕከላት በተቋማት ማቋቋምን ጨምሮ ሴቶችን ተጠቃሚ የሚያደረጉ ሃሳቦች በሚሻሻለው የመንግሥት ሠራተኞች ረቂቅ አካቷል፡፡ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ መንግሥት አልማው እንደሚሉት፣ የህፃናት ማቆያ አገልግሎት መሽጫ ማዕከላት በተቋማት እንዲዘጋጅ መደረጉ በሴት ሠራተኞች የሃሳብና ተያያዥ ጫናዎችን በመቀነስ ምቹ የሥራ ቦታ ለመፍጠር ያስችላል ብለዋል፡፡
ይህ አዋጅ ወላጆች በተለይም እናቶች ከህፃን ልጆቻቸው ርቀው የማይሠሩ በመሆናቸው በሥራቸው ተወዳዳሪና በቂ እንዲሆኑ እንደሚረዳም ተጠቁሟል፡፡ ተቋማትም ቢሆኑ በህፃን ልጃቸው ምክንያት በተደጋጋሚ ከሥራ ገበታቸው የሚቀሩ ወላጅ ሴት ሠራተኞቻቸው ቁጥርን በእጅጉ በመቀነስ የሥራና የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትን ያሳድጋላቸዋል፡፡ ረቂቅ አዋጁ ከባለድርሻ አካለት ጋር ውይይት ተደረጎ ግብዓት ከተሰበሰበበት በኋላ በተያዘው ዓመት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ መንግሥት አልማው ተናግረዋል፡፡ በተመሳሳይ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል የህፃናት ማቆያ አገልግሎት መስጫ ማዕከል ማቋቋሚያ የአሠራር መመሪያ መዘርዝርን የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ሚኒስቴር አዘጋጅቷል፡፡ በመዘርዝሩ ውስጥ ከተካተቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ውስጥም የማዕከሉ ይዘት፣ የሚሰጡ አገልግሎቶች፣ በተጠቃሚዎች ሊሟሉ የሚገባቸው ግዴታዎች ይገኙበታል፡፡
በሚኒስቴሩ የሴቶች ማካተትና ተጠቃሚነት ክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ አሸናፊ ፈይሳ የሚቋቋሙ ማዕከላት በቦርድ እንደሚመሩ የተናገሩ ሲሆን፣ በመንግሥት ተቋማት፣ በልማት ድርጅቶችና ኢንዱስትዎች የሚሠሩ ሠራተኞችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡ ከላይ በተጠቀሱት ተቋማትም እናት ሠራተኛ ባትሆን እና አባት ግን በተቋማቱ ሠራተኛ ከሆነ አገልግሎቱን የሚያገኝ ይሆናል፡፡ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር አዋጁን በያዝነው ዓመት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ አመላክቷል፡፡