24 May 2021 Written by 

ከመጋረጃ ጀርባ የሚሰጥ ምስክርነት ከሕገ መንግሥቱ አንፃር

 

 

ይህንን ርዕሰ ጉዳይ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው እና በወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው እየታዩ የሚገኙ ዜጎች የፍ/ቤት ውሎ ላይ በተደጋጋሚ "ከመጋረጃ ጀርባ ምስክር" እንዲሰማ ፍ/ቤቱ ፈቃድ ሰጠ የሚሉ እና የመሳሰሉት ዘገባዎች መበራከታቸውን ተከትሎ ከአድማጭ በመጣ ጥያቄ መሰረት በኢትዬ FM 107.8 ላይ አጭር ትንታኔ ሰጥቼበታለው። ይሁን እንጂ ከጉዳዩ ወቅታዊነት አንፃር ሰፋ ብሎ በፅሁፍ መልክ ለአንባቢ ቢደርስ ብዙ ብዥታዎችን ያጠራል ብዬ በማመኔ እነሆ ጀባ ብያለው።


መግቢያ

በወንጀል ጉዳይ ወደትክክለኛ ፍትህ ለመድረስ ምስክሮች ያላቸው ሚና የማይተካ ነው። አንድ ድርጊት ተፈፅሟል ወይስ አልተፈፀመም የሚለውን ሊያስረዳ የሚችለው ጉዳዩ ሲፈፀም ያየ ሰው ስለሆነ ትክክለኛ ፍትህ በመስጠት ሂደት ውስጥ የምስክሮችን ሚና የማይተካ ያደርገዋል፣ ይሁን እንጂ ሰዎች የሚደርስባቸውን ተፅዕኖ ፍራቻ ያዩትን እና የሚያውቁትን መስክሩ ሲባሉ አብዛኛውን ጊዜ ያመነታሉ፣ አንዳንዶቹ ፍ/ቤት ስላዘዛቸው ብቻ የግዳቸውን ቀርበው ይናገራሉ ነገር ግን ነገ አብሬው ከምኖር ሰው አልቀያየምም በሚል እውነታውን ከመመስከር ሲቆጠቡ ይስተዋላሉ።

የምስክሮች ጥበቃ ምንነት


ምስክሮች ወይም የወንጀል ጠቋሚዎች በምስክርነታቸው ወይም በጠቋሚነታቸው ምክንያት በቀጥታ ይሁን በተዘዋዋሪ ከሚደርስባቸው አደጋ እና ጥቃት ለመከላከል ሲባል የሚወሰድ እርምጃ ነው።


የምስክሮችን ደህንነት መጠበቅ በወንጀል የፍትህ ስርዓት ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለው ይታመናል። ከእነዚህም መካከል የወንጀል ድርጊቶች እንዳይፈፀሙ እና ተፈፅመው ሲገኙም ፈፃሚዎች ሆኑ ወንጀላቸው ተደብቀው እንዳይቀሩ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው። ይሁን እንጂ ለምስክር ጥበቃ ተብለው የሚወጡ ህግጋት እና እነርሱን ተከትለው የሚወሰዱ እርምጃዎች ትክክለኛ ፍትህ በመስጠት ሂደት ውስጥ የሚያመጡት አሉታዊ ተፅዕኖ አለ። የተጠርጣሪዎችን በግልፅ ችሎት የመሰማት እና የሚቀርቡባቸውን ማናቸውንም ማስረጃዎች የመመልከት ህገመንግስታዊ መብታቸውን ይሸረሽራል በማለት ማዕቀፉን የሚነቅፉ ምሁራን አልጠፉም።

ለምስክር ጥበቃ ሲባል የሚወሰዱ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?


ለምስክር ጥበቃ ሲባል ሃገራት በህግ ማዕቀፎቻቸው የተለያዩ ድንጋጌዎችን ያስቀምጣሉ። ኢትዮጵያም በ2003 ዓ.ም በፌደራል ደረጃ የወንጀል ምስክሮች እና ጠቋሚዎች አዋጅ ቁ.699/2003 የሚሰኝ ህግ አውጥታ እየተገበረች ትገኛለች። ይህ አዋጅ ምስክሮችን ለመጠበቅ ሲባል ሊወሰዱ ስለሚችሉ ተግባራት የደነገገውን እነሆ:-


ሀ/ የአካልና የንብረት ጥበቃ
ለ/ የመኖሪያ ስፍራ መቀየርን ጨምሮ ደህንነቱ የተጠበቀ የመኖሪያ ቦታ መስጠት
ሐ/ ማንነትን እና የባለንብረትነትን መደበቅ
መ/ ማንነትን መቀየር
ሠ/ ለራስ መጠባበቂያ የነፍስ ወከፍ መሳሪያ መስጠት
ረ/ መረጃ በተሰጠበት የወንጀል ድርጊት ያለመከሰስ
ሰ/ መረጃ በሚሰጥበት የወንጀል ጉዳይ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊትም ሆነ በኋላ ተከሳሽ በጥበቃ ተጠቃሚው መኖሪያ ወይም የስራ ቦታ ወይም ት/ቤት አካባቢ እንዳይደርስ ማገድ
ሸ/ የፍርድ ሂደት ተጀምሮ ምስክርነት እስኪሰጥ ድረስ የምስክር ማንነት እንዳይገለፅ ማድረግ
ቀ/ ምስክርነት በግልፅ ችሎት እንዲሰጥ ማድረግ
በ/ ምስክርነት በአካል ሳይታይ ከመጋረጃ በስተጀርባ ሆኖ ወይም ማንነትን በመሸፈን እንዲሰጥ ማድረግ
ተ/ ማስረጃ በኤሌክትሮኒክስ ወይም በሌላ የተለየ ዘዴ እንዲቀርብ ማድረግ፣
ቸ/ በሚስጥር መያዝ ያለበት ካልሆነ በስተቀር ለጠቋሚው ጥቆማ ባቀረበበት ጉዳይ ላይ ወቅታዊ መረጃና ምክር መስጠት፣
ኀ/ እንዲመሰክር ለተጠራ ምስክር የጉዞ እና የውሎ አበል መስጠት
ነ/ የጥበቃ እርምጃው የመኖሪያ ስፍራን ለውጥ ካስከተለ የጓዝ ማንሻ ወጪን መሸፈን
ኘ/ በበቀል የተወሰደ አስተዳደራዊ እርምጃ እንዲታገድ ወይም እንዲሻር ማድረግ
አ/ በበቀል እርምጃ ለደረሰ ጉዳት የህክምና አገልግሎት በመንግስት ሆስፒታል በነፃ መስጠት
ከ/ በጥበቃ እርምጃው ምክንያት ለደረሰ ገቢ ማጣት ወይን በበቀል እርምጃው ለደረሰ የመስራት ችሎታ ማጣት የመሰረታዎ ፍላጎት ማሟያ ወጪን መሸፈን
ኸ/ በጥበቃ ስር እያለ ለደረሰ ሞት የቀብር ማስፈፀሚያ ወጪን መሸፈንና ለቤተሰብ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ፣
ወ/ የጥበቃ ተጠቃሚው የስራና የትምህርት እድል እንዲያገኝ መርዳት፣
ዘ/ ለምስክሩ ወይም ለተጠቃሚው የምክር አገልግሎት መስጠት ወይም እንዲያገኝ ማድረግ

የምስክሮች ጥበቃ ከህገመንግስቱ አንፃር


ምስክሮች በፍትህ ስርዓቱ የገዘፈ ሚና ቢኖራቸውም ህገመንግስታዊ ከለላን አላገኙም። ለዚህም ማሳያ የሚሆነው ህገመንግስቱ አንቀፅ 20(1) ላይ ለተከሰሱ ሰዎች ደህንነት ሲባል የፍርድ ቤት ክርክሮች ለህዝብ እና ለሚዲያ ዝግ በሆነ ችሎት ማካሄድ እንደሚፈቀድ ቢያስቀምጥም ለምስክሮች ጥበቃ እና ደህንነት ሲባል እንዲህ አይነቱ ስርዓት መፈቀዱን አያመለክትም። ይህ ማለት ዝግ ችሎት ከሚፈቀድባቸው 3 ምክንያቶች ውስጥ "ለምስክሮች ጥበቃ ሲባል" የሚለው ምክንያት አልተካተተም ማለት ነው።

 
ሌላው ደግሞ ህገመንግስት አንቀፅ 20(4) ላይ ማንኛውም ተጠርጣሪ የቀረቡበትን ማንኛውንም ማስረጃዎች የመመልከት መብት እንዳለው ይደነግጋል። ማንኛውም ምስክር ማለት የሰው ማስረጃን ማለትም ምስክርን የሚያካትት ስለመሆኑ የሚያከራክር አይደለም። ይሁን እንጂ የምስክር ጥበቃ አዋጁ መሰረት ተከሳሽ በራሱ ላይ የቀረበው የሰው ማስረጃ (ምስክር) መመልከት እንዳይችል ተደርጎ ከመጋረጃ ጀርባ ድምፃቸውን ብቻ እየሰማ መመስከራቸው ተግባሩን ወይም ድንጋጌውን ህገመንግስታዊ ድጋፍ ሊያሳጣው የሚችል ነው።
ሌላው በህገመንግስቱ በየትኛውም ክፍል ላይ ለምስክር ጥበቃ ሲባል መደረግ ስለሚችል የተለየ አሰራር የሚሰጠው ምንም አይነት እውቅና አለመኖሩን ልብ ይሏል።

 

ከመጋረጃ ጀርባ የሚሰጥ ምስክርነት


ከላይ በተገለፁት ንዑስ ርዕሶች ለማሳየት እንደተሞከረው ምስክሮችን ለመጠበቅ ከሚሰወዱ ተግባራት መካከል በምስክር ጥበቃ አዋጁ አንቀጽ 4 (በ) ላይ የተመላከተው ከመጋረጃ ጀርባ የሚሰጥ ምስክርነት አንዱ ነው። እንዲህ አይነቱ ምስክርነት ፍ/ቤት ሊፈቅድ የሚችለው ምስክሮች በግልፅ ተጠርጣሪ ወይም ሌላ ሶስተኛ ወገን እያያቸው ቢመሰክሩ በደህንነታቸው ላይ ጉዳት ሊደርስ ይችላል ብሎ ሲያምን እና የሚመሰክሩበት የወንጀል መተላለፍ ተጠርጣሪውን 10 ዓመት እና ከዚያ በላይ ሊያስቀጣ የሚችል ከባድ ጥፋት መሆኑ ሲረጋገጥ ነው።


ይህ አይነቱ የምስክር ጥበቃ ስርዓት በአብዛኛው አስገድዶ መድፈር ላይ የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑ የግል ተበዳዮች ማንነታቸው ለህዝብ ይፋ ከሆነ ለወደፊት ህይወታቸው መጠቋቆሚያ እንዳይሆኑ እና የትዳር እና የወሲብ ህይወታቸው ላይ ሊፈጠር የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቀነስ ሲባል በሌላ ክፍል ውስጥ ሆነው በድምፅ ማጉያ የምስክርነት ቃላቸውን እንዲሰጡ ይደረጋል። በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ግለሰቦች ከህዝባዊ አመፅ ጋር ስማቸው ተያይዞ በወንጀል ሲጠረጠሩ የወንጀል ተሳትፏቸውን የሚያውቁ ሰዎች በድፍረት እንዲመሰክሩ እና ከተጠርጣሪዎቹ ደጋፊዎች ዘንድ ሊደርስባቸው የሚችልን ጥቃት ለመከላከል በሚል ከመጋረጃ ጀርባ እንዲመሰክሩ ይደረጋል።

 
ከዚህ ጋር ተያይዞ በ1978 እ.አ.አ. በደቡብ አፍሪካ የተከሰተ ጉዳይን እናንሳ ነገሩ እንዲህ ነው:- የANC (የአፍሪካ ብሄራዊ ኮንግረስ) ፓርቲ አባላት የነበሩ ሰዎች የፓርቲው አመራሮች በወንጀል ሲከሰሱ ምስክር በመሆን ፍ/ቤት ቀርበው ቃላቸውን ይሰጣሉ በዚህም መሰረት በርካታ የፓርቲው አመራሮች ለእስር ተዳረጉ። ይህ አካሄድ ያስቆጣቸው የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ምስክር ሆነው ፍ/ቤት የሚቀርቡ እና መረጃ ለመንግስት የሚያቀብሉ የፓርቲው አባላትን "ከሃዲዎች" ናቸው በማለት በተገኙበት እንዲገደሉ መቀስቀሳቸውን ተከትሎ በርካቶች ደመከልብ ሆነዋል።

ምስክርነት ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰጥ የመወሰን ስልጣን ያለው ምን ነው?

ይህ ጥያቄ አከራካሪ ነው፡፡ የተከሳሽ ጠበቆች የፍ/ቤት ስልጣን ነው በማለት ሲከራከሩ አቃቤ ህግ ደግሞ የማቀርባቸውን ምስክሮች ያለባቸውን የደህንነት ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት ከመጋረጃ ጀርባ አሊያም በዝግ ችሎት መመስከር እንዲችሉ የመወሰን ስልጣን የእኔ ነው በማለት ክርክር ያቀርባል፡፡ እንደ ህግ ሆኖ ማገልገል ባይችልም በዚህ ጉዳይ የፌደራል ጠ/ፍ/ቤት በእነ ጃዋር መሃመድ መዝገብ ላይ ግንቦት 11 ቀን 2013 ዓ.ም የሰጠውን ብይን ስንመለከት ምስክሮች በግልፅ ችሎት ይመስክሩ አሊያም ከመጋረጃ ጀርባ የሚል ውሳኔ የመስጠት ስልጣን የፍ/ቤቶች እንደሆነ አስቀምጧል፡፡


ማጠቃለያ


የምስክር ጥበቃ ለወንጀል ፍትህ ስርዓቱ ያለው አስተዋፅኦ ከፍተኛ ቢሆንም ተግባር ላይ ሲውል የተጠርጣሪዎችን መብት በሚያጣብብ መልኩ ሊሆን አይገባም። ከመጋረጃ ጀርባ የሚሰጥ ምስክርነትም ይሁን ሌሎች በምስክር ጥበቃ አዋጁ የተመላከቱ የጥበቃ አይነቶች ህገመንግስታዊ መሰረት ሊኖራቸው የተገባ በመሆኑ ህግ አውጪው አካል ሊያስብበት ይገባል። ከዚህ በተጨማሪ የዝርዝር ህግጋቱ አስፈላጊነት የሚታመንበት ሆኖ ከተገኘ ህገመንግስት በማሻሻል ሂደቱ ውስጥ የወንጀል ምስክር እና ጠቋሚዎች ጥበቃ እውቅና የሚያገኝበትን አንቀጽ ማካተት ለይደር የማይተው እርምጃ መሆኑን መጠቆም እወዳለው።

Last modified on Monday, 24 May 2021 10:49
Abel Zewdu

ጸሐፊው በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ያገኙ ሲሆን ከ5 አመት በላይ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በሕግ ባለሙያነት እንዲሁም በኃላፊነት አገልግለዋል፡፡ ጸሐፊው አሁን ጠበቃና የሕግ አማካሪ ሲሆኑ በተጨማሪም በኢትዮ ኤፍ ኤም 107.8 ላይ በየሳምንቱ አርብ ጠዋት የሚቀርብ "ሕጉ ምን ይላል" የተሰኘ ፕሮግራም እያሰናዱ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡