በሔግ ኔዘርላንድ ውሳኔ የተሰጠው የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ጉዳይ በሰበር ሰሚ ችሎት ሊታይ ነው

Jun 06 2016

 

የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር ኩባንያ 20 ሚሊዮን ዩሮ ዋጋ ባለው የግልግል ክርክር በሔግ የተወሰነበት ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት እንዲከልሰው ጠበቆቹ ያቀረቡት አቤቱታ ተቀባይነት አገኘ፡፡

... 2006 በተፈረመ ስምምነት መሠረት በአውሮፓ ልማት ፈንድ የፋይናንስ ድጋፍ የጥገና ሥራ ለመሥራት የተስማማው የጣሊያን ኮንትራክተር በምድር ባቡር ድርጅት ላይ ያቀረበው ክስ መቋጫ ለማግኘት ሦስት ዓመት ወስዷል፡፡ ለሰበር ሰሚ ችሎቱ የቀረበው አቤቱታ እንደሚያስረዳው የግልግል ዳኝነት ፓናሉ ሦስት አባላት ነበሩት፡፡ ስፔናዊው ፕሮፌሰር ዴቪድ አሪያስና ፈረንሣዊው ፕሮፌሰር ኤዱዋርዶ ሲልቫ ሮሜሮ ለጣሊያኑ ኮንትራክተር ኮንስታ ጄይቪ ሲወስኑ፣ ኬንያዊው ፕሮፌሰር ጀምስ ጋቲ ግን በውሳኔው ባለመስማማት የልዩነት ሐሳባቸውን በተናጠል አሥፍረዋል፡፡

የምድር ባቡር ድርጅት ጠበቆች አስተያየት ከመስጠት ቢታቀቡም ባለፈው ሳምንት ያቀረቡት  አቤቱታ እንደሚያሳየው፣ ሁለቱ የግልግል ዳኞች በአብላጫ ድምፅ ያሳለፉት ውሳኔ የኢትዮጵያን ሕግ በአግባቡ ያልተረዳና በተሳሳተ መንገድ የተረጎመ ነው፡፡ ይህም እንደ መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንደሚቆጠር ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም እንደ አቤቱታው ገለጻ ውሳኔው የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር ኩባንያ ፍትሐዊ የዳኝነት ሒደት ውስጥ ያላሳለፈ እንደሆነ ይወቅሳል፡፡ ሁለቱ የግልግል ዳኞች የጥቅም ግጭት እንዳላቸውና በዚህም አድሏዊነት እንደተስተዋለባቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደጠቆመው ሰበር ሰሚው ችሎት አቤቱታውን የተቀበለው ሲሆን፣ ሁለቱን ተከራካሪ ወገኖች እስኪሰማ ድረስ የግልግል ውሳኔው እንዲታገድ ወስኗል፡፡ የፍርድ ቤቱ ሰነዶች እንደሚያሳዩት ጉዳዩ የታየው በፐርማነንት ኮርት ኦፍ አርቢትሬሽን (ፒሲኤ) ቢሆንም፣ የግልግል ትራይቡናሉ ሕጋዊ መቀመጫ አዲስ አበባ ነው፡፡ ትራይቡናሉ የተጠቀመው የኢትዮጵያን ሕግ ሲሆን፣ ይህም ... 2006 ሁለቱ ወገኖች የምድር ባቡር ኩባንያን ለመጠገን ያደረጉት ስምምነት ነው፡፡ የግልግል ዳኝነቱ የተሰጠው በአውሮፓ ልማት ፈንድ የአሠራር ሥነ ሥርዓት መሠረት ሲሆን፣ ይህም የግልግል ዳኝነቱን ውሳኔ በአገሮቹ ከሚሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ጋር በእኩል ደረጃ ያስቀምጣል፡፡

ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ፣ ይህ ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከቀረቡና 100 ሚሊዮን ዩሮ ከጠየቁ ሁለት የግልግል ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ ሌላኛው ሙሉ በሙሉ ውድቅ የተደረገው ጉዳይ የቀረበው በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ላይ ነበር፡፡ የፒሲኤ ድረ ገጽ እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያና ጂቡቲ የተወከሉት መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ባደረገው አዲስ ሎው ግሩፕ ኤልኤልፒ (ኤኤልጂ) ነው፡፡ ኮንስታ ጄይቪና እህት ኩባንያው ማቲዮሊ ጄይቪ ደግሞ በጣሊያን የሕግ ኩባንያ ተወክለዋል፡፡

ኤኤልጂ በቅርቡ የኢትዮጵያ ማዕድን ሚኒስቴር ከቻይና የነዳጅ ኩባንያ ፔትሮትራንስ ጋር ያደረገውን 1.4 ቢሊዮን ዶላር ክርክር ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታውን ያቀረቡት / ዘውድነህ በየነ ኃይሌ ታዋቂ የሕግ ባለሙያና ልምድ ያካበቱ ናቸው፡፡ ችሎቱ ውሳኔ ለመስጠት የሚወስድበት ጊዜ አልታወቀም፡፡  

Read 50613 times Last modified on Jun 06 2016
Abyssinia Law | Making Law Accessible!

Abyssinia Law is  a legal resource portal providing open access to primary and secondary legal materials for Ethiopia, such as laws, court decisions, articles, contact guidance and Lawyers Directory - with texts supplemented by online videos, a discussion forum and user blog. The service gives free access to Federal and State consolidated laws of Ethiopia (with status information whether the law is amended, repealed or effective)